የሐፍስ ቂርኣት ተዓማኒ አይደለምን ?
ከዓሲም ኢብን አቢ ነጁድ ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኢማሙ ሐፍስ ኢብኑ ሱለይማን በሐዲስ ሊቃውንት ዘንድ መትሩክ በመሆኑ የእርሱ የቁርኣን ንባብ ተዓማኒ አይደለም በማለት የሙርተዶችን ተራ ክስ የሚያራግቡ ክርስቲያን ሚስዮናውያን ዛሬ ላይ እንደ መከራከሪያ ነጥብ ሲያነሱት ይታያሉ። እንደው የሐፍስ ሪዋያ ተዓማኒ አይደለም ራሱ ብንል ይህ ከቁርኣን ታሪካዊ ተዓማኒነት ጋር ምን አገናኘው ? ምክንያቱም ቁርኣን በአንድ ቃሪዕ (አንባቢ) ብቻ የተላለፈ አይደለምና።
ዛሬ በስፋት የሚታወቀው የሐፍስን ሪዋያ ከዓሲም ኢብኑ አቢ ኑጁድ የተቀበለው ሰው ሐፍስ ኢብኑ ሱለይማን ብቻ ሳይሆን አቡበከር ኢብኑ አቢ አያሽ፣ አቡ ዐምር ኢብኑ አለዕ፣ ኸሊል ኢብኑ አህመድ እና ሌሎችም ብዙ ተማሪዎች ቂርኣቱን ከዓሲም ተምረዋል፣ የሐፍስን ሪዋያ ከዓሲም የተቀበለው ሐፍስ ኢብኑ ሱለይማን ብቻ ባለመሆኑ እርሱ መትሩክ ቢሆንም ሪዋያው ሙተዋቲር በመሆኑ በጭራሽ የሚተች አይደለም። ኢማም ሐፍስ በዒልሙል አሃዲስ ይህን ያህል የሚባል እውቀት ባይኖረውም (ከ ሪጃሉን ሢቀት ባይቆጠርም) በቂርኣት ግን ተፎካካሪ ያሌላው አንባቢና መምህር እንደሆነ በቀደምት ሊቃውንት የተመሰከረለት ቃሪዕ ነበር።
ኢማሙ ዘሀቢይ ስለ ሐፍስ ሲናገር እንዲህ ይላል:- ‟ሐፍስ በሐዲስ ላይ ብዙም ባይሆንም በቂርኣት ላይ ግን እጅግ ተዓማኒ (Reliable) እና ፅኑ ነበር [ጠበቃት አል-ቁራ 140] በሌላም ቦታ ላይ እንዲህ በማለት ተናግሯል ‟ሐፍስ በቁርኣን ታማኝ ቃሪዕ (አንባቢ) ቢሆንም ሐዲሳትን በማስተላለፍ ላይ ግን ደካማ ነበር ምክንያቱም እርሱ የተካነው በቂርኣት እንጂ በሐዲስ አይደለምና፣ ከዚያ ውጪ እርሱ (ሐፍስ) ትክክለኛ ሰው እና ታማኝ ነበር።
[ሚዛን አል-ኢዕቲዳል ፊ ነቅድ አል-ሪጃል 2:319 ቁጥር 2124]
የሕያ ኢብኑ ሙዒንም እንዲህ በማለት ተናግሯል ‟ሐፍስ ኢብኑ ሱለይማን እና አቡበከር ኢብኑ አያሽ ከዓሲም ኢብኑ ኑጁድ በመጣው ሪዋያ (ቂርኣት) ዙርያ ከሌሎቹ ተማሪዎች በላይ የበለጠ እውቀት ነበራቸው። ኢማሙ ሐፍስ ሪዋያውን በማስተላለፍ ረገድ ታማኝ ቢሆንም በሐዲስ ደካማ ነበር፣ አቡበከር ደግሞ በዚህ ከእርሱ ይልቅ እውነተኛ ነው።”
[ተህዚብ አልከማል ፊ አስማዕ አል-ሪጃል 7:15 ቁጥር 1390]
ኢማም አቡበከር ኻቲብ አል-በግዳዲም በርዕሱ ላይ እንዲህ ይላሉ ‟የቁርኣን ቀደምት ሊቃውንት ሐፍስ ቂርኣትን በማስተላለፍ ረገድ ከአቡበክር ቢን አያሽ የበለጠ ታማኝ እና ትክክለኛ መሆኑን ገልጸዋል።”
[ታሪኽ መዲና አል-በግዳድ 8:186-188]
ስናጠቃልል:- ከዓሲም ኢብኑ አቢ ኑጁድ በመምጣት በሐፍስ ኢብኑ ሱለይማን በኩል የተላለፈው የሐፍስ ንባብ ዛሬ እጅጉን በስፋት የሚነበብ ታዋቂ ቂርኣት ነው። ሐፍስ ሐዲሳትን በማስተላለፍ ረገድ ደካማ ከሚባሉት ሰዎች መካከል መሆኑ ጥርጥር የለውም፣ ይሁን እንጂ ቂርኣትን በማስተላለፍ ዙርያ እጅጉን ታማኝ የሆነ ሰው ነው፣ ይህ ደግሞ በቀደምት ሙስሊም ሊቃውንት እንኳ የተመሰከረለት እውነታ ነው። እንደው ሐፍስ በቂርኣት ዙርያ እንኳ ታማኝ አልነበረም ራሱ ቢባል የዓሲምን ቂርኣት ያስተላለፈው ሐፍስ ብቻ ሳይሆን በርካታ ቃሪዖች ይህን የኩፋን ቂርኣት ከመምህራቸው በኩል ተምረው አስተምረዋል፣ ከእነርሱ መካከል ታዋቂው አቡበከር ኢብኑ አቢ አያሽ ነው። ስለዚህ ቂርኣቱ ሙተዋቲር እንጂ አሐድ ባለመሆኑ አንዱን አስተላለፊ በመተቸት ብቻ ዘገባውን ውድቅ ማድረግ አይቻልም። ኢማሙ ሐፍስ በሊቃውንት የተተቸው በሐዲስ ስርጭት እንጂ በቁርኣን ንባብ አይደለም፣ በአጭሩ እውነታው ይህን ይመስላል።
—————————————————